JavaScript is required

ነፃ መዋዕለ ህጻናት (ኪንደር) (About Free Kinder) - አማርኛ (Amharic)

ነፃ የመዋዕለ ህጻናት (ኪንደር) ኣገልግሎት በቪክቶሪያ ውስጥ ባሉ ተሳታፊ የአገልግሎት መስጫዎች ውስጥ ባሉ የሶስት እና የአራት-ዓመት መዋዕለ ህፃናት ወይም በቅድመ-ዝግጅት ፕሮግራሞች ውስጥ ይገኛል። ይህ ሁለቱንም የረጅም (ሙሉ) ቀን እንክብካቤ እና ራሱን የቻለ (የክፍለ ጊዜ ተብሎም ይጠራል) የመዋዕለ ህጻናት (ኪንደር) አገልግሎቶችን ያጠቃልላል።

ለቤተሰቦች ቁጠባ

በተሳታፊ ክፍለ-ጊዜ መዋእለ ህፃናት ውስጥ የተመዘገቡ ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች የነፃ ፕሮግራም ያገኛሉ።

በተሳታፊ የረጅም (የሙሉ) ቀን እንክብካቤ ውስጥ የተመዘገቡ ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች ዓመታዊ የክፍያ ማካካሻ ይቀበላሉ።

የነጻ መዋዕለ ሕጻናት (ኪንደር) ብቁነት

ነፃ መዋዕለ ሕጻናት (ኪንደር) ለሁሉም ሰው ነው።

ቤተሰቦች ለማግኘት ብቁ ለመሆን የጤና እንክብካቤ ካርድ ወይም የጡረታ ካርድ፣ የአውስትራሊያ ዜግነት ወይም የአድራሻ ማረጋገጫ ሊኖራቸው አይገባም። እንዲሁም ነፃ መዋዕለ ሕጻናት (ኪንደር) ለማግኘት ለአውስትራሊያ መንግሥት የሕጻናት እንክብካቤ ድጎማ (CCS) ብቁ መሆን አያስፈልግም።

ነጻ መዋዕለ ህጻናት (ኪንደር) መቀበል የሚችሉት ከአንድ መዋዕለ ህፃናት አገልግሎት ብቻ ነው። የመዋዕለ ሕጻናት (ኪንደር) አገልግሎት ነፃ መዋዕለ ሕጻናት (ኪንደር) የሚያገኙበትን አገልግሎት በመሰየም ደብዳቤ እንዲፈርሙ ይጠይቅዎታል። ልጅዎ ከአንድ በላይ የመዋዕለ ሕጻናት (ኪንደር) አገልግሎት የሚከታተል ከሆነ፣ ነፃ መዋዕለ ሕጻናት (ኪንደር)ን የት ማግኘት እንደሚፈልጉ ለእያንዳንዱ አገልግሎት ማሳወቅ አለብዎት።

ነጻ መዋዕለ ሕጻናት (ኪንደር) የገንዘብ ድጋፍ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል

ነፃ መዋዕለ ሕጻናት (ኪንደር) የሚያቀርቡ የመዋዕለ ሕፃናት አገልግሎቶች በቀጥታ ከቪክቶሪያ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ያገኛሉ። ይህ ማለት ቤተሰቦች የሚመለስላቸው ገንዘብ እንደገና መጠየቅ አያስፈልጋቸውም ማለት ነው፣ ይልቁንስ ይህ ከሚከፍሉት ክፍያ ይቀነሳል። በክፍለ-ጊዜ መዋዕለ ህጻናት (ኪንደር) ፕሮግራሙ ነፃ ነው።

የረጅም ቀን እንክብካቤ መዋዕለ ህፃናት ፕሮግራሞችን የሚጠቀሙ ቤተሰቦች ከነጻ መዋዕለ ሕጻናት (ኪንደር) የሚገኘውን ቁጠባ በእያንዳንዱ የሂሳብ አከፋፈል ሂደት 'የቪክቶሪያ መንግስት ነፃ መዋዕለ ህጻናት (ኪንደር) ማካካሻ' በሚል በክፍያ መጠየቂያዎች ላይ በግልጽ ተሰይሞ ማየት ይችላሉ።

የክፍያው ማካካሻ ከኪስዎ ወጪ በሚደረጉ ክፍያዎች ላይ እንዴት እንደሚተገበር

የነፃ መዋዕለ ህጻናት (ኪንደር) ማካካሻ በዓመት ውስጥ በመደበኛነት በክፍያዎ ላይ ይካተታል (ለምሳሌ በየሳምንቱ ወይም በየሁለት ሳምንቱ)። በክፍያ መጠየቂያ (ኢንቮይስ) ላይ በግልጽ የተቀመጠውን መጠን ‘የቪክቶሪያ መንግሥት ነፃ መዋዕለ ህጻናት (ኪንደር) ማካካሻ’ በሚል ሥር ማየት መቻል አለብዎት።

ማካካሻው በክፍያዎ ላይ እንዴት እንደሚተገበር እና ይህ በክፍያ መጠየቂያዎ ላይ እንዴት እንደሚታይ መረጃ ለማግኘት እባክዎን ከመዋዕለ ሕፃናት አገልግሎትዎ ጋር በቀጥታ ይነጋገሩ። ልጅዎ በሳምንት ከ15 ሰአታት በላይ የሚጠቀም ከሆነ፣ እነዚህ ተጨማሪ ሰአታት በማካካሻ ክፍያው አይሸፈኑም።

ለአውስትራሊያ መንግሥት የሕጻናት እንክብካቤ ድጎማ (CCS) ብቁ ከሆኑ በመጀመሪያ ይተገበራል። ያ ማለት የአውስትራሊያ መንግሥት የሕጻናት እንክብካቤ ድጎማ (CCS) እና የነጻ መዋዕለ ህጻናት (ኪንደር) ማካካሻ ከተካተተ (ከተቀነሰ) በኋላ ብቻ ነው ቀሪውን መጠን መክፈል የሚያስፈልግዎት።

ለምሣሌ፦

  • የ 4 ዓመት ልጅ በሳምንት ለ 3 ቀናት የመዋዕለ ህጻናት (ኪንደር) ፕሮግራም ወዳለው የረጅም (ሙሉ) ቀን እንክብካቤ መስጫ ከሄደ።
  • አገልግሎቱ በሳምንት ለ3 ቀናት (የመዋዕለ ሕፃናት እና ተጨማሪ የእንክብካቤ ሰዓቶችን ጨምሮ) 360 ዶላር ያስከፍላል።
  • ቤተሰቡ በሳምንት የ252 ዶላር ከአውስትራሊያ መንግሥት የሕጻናት እንክብካቤ ድጎማ (CCS) ያገኛል።
  • በ2025፣ አገልግሎቱ የ2,101 ዶላር የነጻ የመዋዕለ ህጻናት (ኪንደር) በ40 ሳምንታት ውስጥ (በየሳምንት 52.53 ዶላር) ማካካሻ ያካትታል።
  • ቤተሰቡ ከአውስትራሊያ መንግሥት የሕጻናት እንክብካቤ ድጎማ (CCS) እና ከነጻ መዋዕለ ህጻናት (ኪንደር) ማካካሻ በኋላ የቀረውን 55.478 ዶላር በሳምንት ይከፍላል።

እባክዎን ያስታውሱ። ይህ ለምሳሌ ብቻ የተቀመጠ ነው፤ ወጪዎች ግን እንደየግለሰቡ ሁኔታ እና አመታዊ የነጻ ኪንደር ማካካሻ መጠን ይለያያል።

Updated