አንድ ላይ፣ ሁሉም ሰው የኔ ነው የሚላቸው፣ የሚማርባቸው እና የሚያድግባቸው ደህንነታቸው የተጠበቀ ትምህርት ቤቶችን እንፈጥራለን።
ትምህርት ቤቶች፣ ቤተሰቦች እና ተማሪዎች አብረው ሲሰሩ፣ የበለጠ ውጤት እናመጣለን። እነዚህ ሽርክናዎች/ግንኙነቶች ሁሉም ተማሪዎች የእኔነት ስሜት እንዲሰማቸው (እንዲቀላቀሉ)፣ እንዲማሩ እና እንዲያድጉ የሚረዱ የት/ቤት አካባቢዎችን ለመፍጠር አስፈላጊ ናቸው። እንደ ወላጅ እና ተንከባካቢ፣ ልጅዎ የሚጠበቅበትን የጋራ ባህሪ እንዲረዳ እና እንዲያሟላ በመርዳት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።
ተማሪዎች የሚጠበቁ ባህሪያትን እንዴት እንደሚያሳዩ
በትምህርት ቤት፣ ሁሉም ተማሪዎች ሰው አክባሪ፣ ደህንነት የሚጠብቁ፣ እና ተሳታፊ እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል። እነዚህ ባህሪያት ትምህርት ቤቶች ሁሉም ሰው ስኬታማ የሚሆንበት ቦታ ለማድረግ ይረዳሉ።
ተማሪዎች አክባሪ፣ ደህንነት የሚጠብቁ እና ተሳታፊ በመሆን እነዚህን የሚጠበቁ የባህሪይ ፍላጎቶች ያሟላሉ።
ሰው አክባሪ
- የሰራተኞች መመሪያዎችን እና የትምህርት ቤት ህጎችን መከተል።
- የትምህርት ቤቱን ንብረት እና የሌሎችን እቃዎች መንከባከብ።
- የአክብሮት ቋንቋ መጠቀም።
ደህንነት የሚጠብቅ
- ራሳቸውን እና ሌሎችን ከጉዳት መጠበቅ።
- እነርሱ ወይም ሌላ ሰው ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ እየተጎዳ ከሆነ መናገር ወይም የአዋቂ/ትልቅ ሰው እርዳታ መጠየቅ።
- ደህንነታቸው የተጠበቀ እና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ብቻ ወደ ትምህርት ቤት ማምጣት።
ተሳታፊ
- በየቀኑ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ፣ በሰዓቱ መገኘት እና ለመማር ዝግጁ መሆን።
- መሳተፍ፣ የቻሉትን ማድረግ እና በሚያስፈልጋቸው ጊዜ እርዳታ መጠየቅ።
- የሞባይል ስልክ ፖሊሲን ጨምሮ የትምህርት ቤቱን ፖሊሲዎች ማወቅ እና መከተል።
ወላጆች እና ተንከባካቢዎች እንዴት መርዳት እንደሚችሉ
አወንታዊ ባህሪን ሞዴል/አርአያ ሆኖ በማሳየት እና በማበረታታት፣ ልጅዎ በትምህርት ቤት ስኬታማ ለመሆን የሚያስፈልጉትን ክህሎቶች እና ልምዶች እንዲገነባ ያግዛሉ። ቤተሰቦች እና ትምህርት ቤቶች አብረው ሲሰሩ፣ ተማሪዎች የበለጠ ውጤት ማምጣት ይችላሉ።
ወላጆች እና ተንከባካቢዎች የልጃቸውን ባህሪ እንደሚከተለው እንዲሆን በመደገፍ ሊረዱ ይችላሉ፡-
ሰው አክባሪ
- የትምህርት ቤቱን ህግጋት ማወቅ እና ቤት ውስጥም መደገፍ።
- ስለ የት/ቤት ሰራተኞች፣ ቤተሰቦች እና ሌሎች በአካል እና በኦንላይን ላይ እንዴት አክብሮት የተሞላበት ባህሪ እንደሚናገሩ አርአያ ሆኖ ማሳየት።
- ችግሮችን ቀደም ብሎ ለማንሳት እና ለመፍታት የትምህርት ቤቱን ሂደቶች መጠቀም።
ደህንነት የሚጠብቅ
- ጉዳዩን ለመረዳት እና ለመፍታት ልጅዎ በትምህርት ቤት ውስጥ ችግር ካጋጠመው ከሰራተኞች ጋር አብሮ መስራት።
- ልጅዎ በትምህርት ቤት ከታመነ አዋቂ እርዳታ መጠየቅ ምንም ችግር እንደሌለው እንዲያውቅ ማድረግ።
- ከልጅዎ ጋር በመነጋገር እና ስጋቶችን ቀድሞ በመፍታት ልጅዎ በኦንላይን ላይ ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ።
ተሳታፊ
- ልጅዎን በየእለቱ ትምህርት ቤት እንዲከታተል መርዳት - እያንዳንዱ ቀን ትርጉም አለው።
- ከትምህርት ቤት ሰራተኞች ጋር መነጋገር እና የልጅዎን ትምህርት እና ደህንነት ለመደገፍ በጋራ መስራት።
- ከልጅዎ ጋር ስለነበረው የቀን ውሎ እና ስሜቱ ማውራት እና እያደረገ ያለው ጥረት እና እድገት እንደተገነዘቡት በመግለጽ መማሩን እንዲቀጥል ማበረታታት።
አንዳንድ ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ትምህርት ቤት መገኘት ትግል ሊሆንባቸው እንደሚችል ወይም ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ እምቢተኝነት ጋር እየታገሉ እንደሆነ እናውቃለን። ሊረዱ የሚችሉ አንዳንድ ግብዓቶች እነሆ፦
ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የሚጠበቅባችው ባህሪ እንዲያሟሉ እንዴት እንደሚደግፉ
አወንታዊ ባህሪን በማስተማር እና በማጠናከር፣ ትምህርት ቤቶች በመማር እና በደህንነት ላይ ያተኮረ አወንታዊ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ፍትሃዊ የመማሪያ አካባቢ እንዲኖሩ ያረጋግጣሉ።
ትምህርት ቤቶች ሰው አክባሪ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ እና ተሳታፊ በመሆን ቤተሰቦችን እና ተማሪዎችን ይደግፋሉ።
ሰው አክባሪ
- የትምህርት ቤት ህጎችን እና የሚጠበቁትን አወንታዊ ባህሪያት ተማሪዎችን ማስተማር እና ማሳየት።
- የሚጠበቀውን የአክብሮት ባህሪ በግልፅ ማስተማር፣ ሞዴል ማድረግ (ማሳየት) እና እውቅና መስጠት።
- ከሁሉም ተማሪዎች፣ ወላጆች እና ተንከባካቢዎች ጋር በትብብር እና በአዎንታዊ መልኩ መሳተፍ።
ደህንነት የሚጠብቅ
- ጉልበተኝነትን ለመከላከል እና ለጉልበተኝነት ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም የተማሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ግልፅ ፖሊሲዎች እና ሂደቶች እንዲኖር ማድረግ።
- ተጨማሪ ድጋፎችን በንቃት ለተማሪዎች መስጠት፣ እና ተማሪዎች እንዲናገሩ እና እርዳታ እንዲፈልጉ መደገፍ።
- በአካል፣ በማህበራዊ እና በባህል ደህንነቱ የተጠበቀ የትምህርት ቤት አካባቢን ለመጠበቅ ችግሮችን በንቃት መለየት እና መፍታት።
ተሳታፊ
- የሁሉንም ተማሪዎች ፍላጎት የሚያሟላ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ አካታች ትምህርት መስጠት።
- ተማሪዎች በትምህርታቸው እና በትምህርት ህይወታቸው ላይ በሚደረጉ ውሳኔዎች ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ማበረታታት።
- ሁሉም ተማሪዎች የታዩ፣ የተሰሙ፣ እና የተከበሩ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ለማድረግ ጠንካራ፣ እምነት የሚጣልባቸው ግንኙነቶችን መገንባት።
የትምህርት መምሪያ አወንታዊ የተማሪ ባህሪን ለመገንባት እና በትምህርት ቤቶች፣ ተማሪዎች እና ቤተሰቦች መካከል አወንታዊ ግንኙነቶችን ለማጎልበት ለትምህርት ቤቶች ግብዓቶችን እና ድጋፍን ይሰጣል።
ወላጆች እና ተንከባካቢዎች እርዳታ ለማግኘት ወዴት መሄድ እንደሚችሉ
የልጅዎ ጤንነት፣ ባህሪ ወይም ደህንነት የሚያሳስብዎት ከሆነ የሚከተሉትን ማድረግ ይችላሉ፡-
- የልጅዎን አስተማሪ ወይም ለዚህ ጉዳይ የተመደበውን ሰው እንደ መጀመሪያው ደረጃ ያነጋግሩ እና ስጋቶችን ለማሳወቅ የትምህርት ቤቱን ሂደት ይከተሉ።
- ትምህርት ቤቱን ለድጋፍ ወይም ለሪፈራል ይጠይቁ - ከደህንነት ሰራተኞች ወይም ከልዩ ባለሙያ አገልግሎቶች ጋር ሊያገናኙዎት ይችላሉ።
- ተጨማሪ እርዳታ ከፈለጉ የትምህርት መምሪያን የክልል ቢሮ ያነጋግሩ።
የሚከተሉት ግብዓቶችም ይገኛሉ፡-
- ሬዚንግ ቺልድረን ኔትዎርክ/Raising Children Network - ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ፣ ቅድመ-ታዳጊዎች እና ታዳጊዎች ላሏቸው ወላጆች ምክር ይሰጣል።
- የኢሴፍቲ ኮሚሽነር - የህጻናትን ደህንነት በኦንላይን ላይ ለመጠበቅ ለወላጆች እና ተንከባካቢዎች ምክር ይሰጣል።
- ዘረኝነት ሪፖርት ማድረጊያ ቀጥተኛ የስልክ መስመር - በትምህርት ቤቶች ውስጥ ዘረኝነትን ወይም የሃይማኖት መድልዎ እንዴት ሪፖርት ማድረግ እንደሚቻል ይወቁ።
- ቡልይ ስቶፐርስ/Bully Stoppers - ስለ ጉልበተኝነት ለወላጆች እና ተንከባካቢዎች ምክር ይሰጣል።
Updated